በአሁኑ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ ችግር ውስጥ ናቸው። መንግስት በተለይ በከተሞች አካባቢ እጅግ ደሃ ለሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች በነጻ የመመገቢያ ጣቢያዎችን በማቋቋም በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ምግብ እንዲመገቡ እያደረገ ነው። በከተሞች አካባቢ ያለው አብዛኛው ህዝብ ለቤት ኪራይ እየከፈለ ነው የሚኖረው፤ ሆኖም የዚህ ኪራይ ክፍያ በየጊዜው እየጨመረ በመሄዱ እጅግ ለብዙዎች ኑሮን አስከፊ የሚያደርግባቸው ተጨማሪ ምክንያት ሆኖባቸዋል። ሰዎች ተቀጥረውም ሆነ በግላቸው ስራ ሰርተው የሚያገኙት ክፍያ ብዙ መስኮት ላለው ወጪያቸው መሸፈኛ ለመሆን ብቃት እያጣነው። በየዕለቱ እየከፋ ያለው የዋግ ግሽበትም እንዲሁ ለዜጎች ከባድ ራስ ምታት መሆኑን ቀጥሏል። ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ግን የሰዎች በበጀት እቅድ አለመመራትም ለችግሮቹ መባባስ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ሊካድ አይችልም። በዚህ አጠር ያለ ጽሁፋችን ከዚህ የከፋ የገንዘብ ችግር በመጠኑም ቢሆን ሊያግዟችሁ ሰለሚችሉና ዛሬውኑ ተግባራዊ ልታደርጓቸው ስለሚገቡ የበጀት ጥቅሞች ጥቂት ጠቃሚ ጥቆማዎችን ልናመለክታችሁ ወደናል።
Contents
- 1 የበጀት ጥቆማ #1: በጀትን በጋራ ማውጣት ወይም ማቀድ
- 2 የበጀት ጥቆማ #2: ከዜሮ በመነሳት በጀትን ማውጣት ወይም ማቀድ
- 3 የበጀት ጥቆማ #3: በቅድሚያ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ዝርዝሮች ጀምሩ
- 4 የበጀት ጥቆማ #4: ክሬዲት ካርዳችሁን ወይም የኤቲኤም ካርዳችሁ ካዝናችሁ ወይም ካቢኔታችሁ ውስጥ ቆልፉበት
- 5 የበጀት ጥቆማ #5: ሁሌም በወሩ አጋማሽ ላይ ስብሰባ አካሂዱ
- 6 የበጀት ጥቆማ 6: አካሄዳችሁን ወይም እርምጃችሁን ተከታተሉ
- 7 የበጀት ጥቆማ 7: ሁሌም በበጀት ከያዛችሁት የገንዘብ መጠን በታች ወጪ ለማድረግ ሞክሩ
- 8 ማጠቃለያ
የበጀት ጥቆማ #1: በጀትን በጋራ ማውጣት ወይም ማቀድ
ባለትዳሮች ከሆናችሁ በጀታችሁን አብራችሁ በጋራ እንድትሠሩ እንመክራለን። በየወሩ ያለፈውን ወር አፈጻጸም የምትወያዩበት የቤተሰብ ስብሰባ ማድረግ እና የሚቀጥለውን ወር በጀት ማውጣት አለባችሁ። ለዚህ የቤተሰብ ስብሰባ አብሮ የመቀመጥ ግቡ ያለፈው ወር እንዴት እንደሄደ እና በአዲሱ ወይም በቀጣዩ ወር ምን ምን ማስተካከል እንደምትችሉ ለመወያየት ማስቻል ነው። ትዳር ያልመሰረታችሁ ከሆነ፣ በክፉም ሆነ በደጉ ከእናንተ ጎን የሚሆንና የሚያስብላችሁን ሰው ማግኝት እንዳለባችሁ እንመክራለን።
የበጀት ጥቆማ #2: ከዜሮ በመነሳት በጀትን ማውጣት ወይም ማቀድ
በኩባንያዎች በብዛት ትቅም ላይ የሚውል ዘዴ ቢሆንም እናንተም በቤተሰብ ደረጃ ልትገለገሉበት የምትችሉት ነው። በዜሮ ላይ በተመሰረተ በጀት (ZBB) አሰራር መሰረት፣ በጀታችሁን ከምንም ወይም ከባዶ በመነሳት መጀመር አለባችሁ። ይህን አካሄድ የመጠቀም ግቡ ገና ወሩ ሲጀምር ሁሉንም የቤተሰባችሁን ወጪዎች መሸፈናችሁን ማረጋገጥ ነው። እንደ ቁጠባ እና ልዩ ልዩ ነገሮችን በበጀታችሁ ውስጥ ማካተታችሁን ልብ ማለትም ተገቢ ነው። ቤተሰብ እንዳለው ሰው፣ በየወሩ ገንዘብ ለመቆጠብ በሚያስችል መልኩ ሁልጊዜ በጀታችሁን ማሰናዳትና መመራት አለባችሁ። የምትቆጥቡት ገንዘብ የግድ ከፍ ያለ መሆንም የለበትም። ልዩ ልዩ በሚል የበጀት ርዕስም ስር የምትይዙት ገንዘብ በድንገት ለሚከሰቱ ጉዳዮች መሸፈኛ ሊሆን ይችላል።
የበጀት ጥቆማ #3: በቅድሚያ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ዝርዝሮች ጀምሩ
በቤተሰባችሁ በጀት ውስጥ ያሉት እቃዎች ወይም ጉዳዮች እንደ አስፈላጊነታቸው ወይም ወሳኝነታቸው መመደብ አለባቸው፣ አለያም ደረጃ ሊሰጣቸው ይገባል። እንደ ቤተሰብ፣ የግድ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የቤት መግዣ ወይም ኪራይ፣ ምግብ እና ነዳጅ ናቸው። ያለ ገመድ፣ ሌሎች ነገሮች አሉ እንደ ልብስ፣ የስልክ ወጪዎች እና ለበጎ አድራጎት የሚደረጉ ልግስናዎች ያሉ ለጊዜው አንገብጋቢ ያልሆኑ። ልብስ ስንል ግን በየወሩ እሱን መግዛት አያስፈልግም ለማለት መሆኑ ሊታወስ ይገባል። ለበጀታችሁ የቅድሚያ ደረጃዎችን መስጠት ከየትኛው በጀት ላይ እንደሚቆረጥ ወይም እንደሚቀነስና የትኛው ላይ ደግሞ እንደምትጨምሩ ለማወቅ ይረዳችኋል።
የበጀት ጥቆማ #4: ክሬዲት ካርዳችሁን ወይም የኤቲኤም ካርዳችሁ ካዝናችሁ ወይም ካቢኔታችሁ ውስጥ ቆልፉበት
ክሬዲት ካርድ ወይም የኤቲኤም ካርድ ብዙ ቤተሰቦችን አበላሽቷል ማለት ይቻላል። ይህ የሆነበት ምክንያትም በተለይ ከበጀታችሁ በላይ በምትሄዱበት ጊዜ የማትፈልጓቸውን ዕቃዎች የመግዛት ልማድ ነው እያመጣ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የክሬዲት ካርድ ወይም የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጠቅላላው ህዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ገና እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ተጠቃሚ በሆኑ ሰዎች ዘንድ ግን ይህ የጠቀስነው ልማድ ስር እየሰደደ መምጣቱ አሌ አይባልም። ስለሆነም ከበዛ የክሬዲት ካርድ ዕዳ ራሳችሁን ነጻ ለማድረግ ሁነኛው መላ የክሬዲት ካርዳችሁን ካዝናችሁ ውስጥ በመቆለፍ ቁልፉን ወዳጃችሁ ጋር እንዲቀመጥ ማድረግ ነው።
የበጀት ጥቆማ #5: ሁሌም በወሩ አጋማሽ ላይ ስብሰባ አካሂዱ
ኩባንያዎች በየወሩ ብዙ ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይም የአሰራር ስልቶቻቸውን ወይም ስትራተጂዎቻቸውን መለስ ብሎ ለማየትና የእቅዶቻቸውን አካሄና እርምጃዎችም ይገመግማሉ። እነዚህ ስብሰባዎች መኖራቸው እርምጃዎቻቸውን እንዲከታተሉ እና ተገቢ የሆኑ ለውጦችንም እንዲያደርጉ ያስችሏቸዋል። ስለዚህ፣ እናንተም ልክ እነዚህ ኩባንያዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በየወሩ አጋማሽ ላይ ስብሰባ በማድረግ እርምጃችሁን መለስ ብላችሁ እንድታዩና እንድትገመግሙ እንመክራለን። ይህ ስብሰባ አጠር ያለ ጊዜ ብቻ መውሰድ የሚገባው ከመሆኑም ባሻገር በበጀት እቅዳችሁ መሰረት እየፈጸማችሁ መሆን አለመሆኑን ለመመልከትና አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችንም የምታደርጉበት ይሆናል።
የበጀት ጥቆማ 6: አካሄዳችሁን ወይም እርምጃችሁን ተከታተሉ
ቀደም ባለው ጊዜ ባቀረብንላችሁ ጽሁፎች እርምጃችሁን ወይም አካሄዳችሁን ለመከታተል እንዲረዳችሁ ወረቀት ላይ ተገቢ ዝርዝሮችን እንድታሰፍሩ ምክር እንደሰጠን የምታስታውሱ ይመስለናል። አሁንም ይህን ማድረግ መቻላችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወጪዎቻችሁን ለመከታተል የሚያስችሏችሁን በርካታ የኦንላይን መሳሪያዎችን ወይም መገልገያዎችን እንድትጠቀሙ እንመክራለን። እነዚህ እነዚህ መተግበሪያዎች ከበጀታችሁ በላይ ወጪዎችን ስታወጡ ማሳወቂያዎችን የሚልኩላችሁ ከመሆኑም ሌላ የት ላይ እንደተሳሳታችሁ ይነግሯችኋል። በእነዚህ መተግበሪያዎች፣ ወጪዎቻችሁን መለስ ብሎ ለመከታተል ጥሩ አጋጣሚ ይሆኗችኋል። ከእነዚህ ምርጥ ከሆኑት መገልገያዎች መካከል ጥቂቶቹ: Birr How to Save Money እና Mint ይገኙበታል።
የበጀት ጥቆማ 7: ሁሌም በበጀት ከያዛችሁት የገንዘብ መጠን በታች ወጪ ለማድረግ ሞክሩ
በጀት በቀላሉ ሊያወጡት ያሰቡትን መነሻ የሚያቀርብ መሳሪያ ነው። ከበጀት በላይ እንዲወጡ ሁልጊዜ የማይመከር ቢሆንም፣ በምትችሉበት ጊዜ ሁሉ ቁጠባ ለማድረግ መሞከር አለባችሁ። ለምሳሌ፣ ለወር ነዳጅ 1000 ብር በጀት መድባችሁ ሳለ ያወጣችሁት ግን 800.00 ብር ከሆነ በዚህ ደስተኛ መሆን አለባች- ከበጀታችሁ ያነሰ የገንዘብ መጠን ለማውጣት ችላኋችልና።
ማጠቃለያ
በጀት በእቅድ አለመያዝ ወይም አለመከተል ብዙ ሰዎች ከሚፈፅሟቸው በጣም የተለመዱ ስህተቶች መካከ ሁለቱ ናቸው። በአገረ አሜሪካ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ለምሳሌ ከ 3 አሜሪካውያን አንዱ በጀት እንደማይመራ አስታውቋል። ይህ ግን ፈጽሞ የማይመከር ጉዳይ ነው። እናንተ ዛሬውኑ በበጀት መመራት መጀመር አለባችሁ። ይህንን ማድረጉም ትክክለኛ የፋይናንስ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ይረዳችኋል።