ገንዘብ ነክ የሆኑ ስህተቶችን ስለማስወገድ

ትርጉሞች:
en_USsw

ሰዎች በህይወታቸው የሆነ ጊዜ ላይ ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጭንቀት ውስጥ የመዘፈቅ አደጋ ያጋጥማቸዋል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ መነሻ ምክንያታቸው በቀጥታ አንዳንድ ገንዘብ ነክ ስህተቶችን በመፈጸማቸው የተነሳ ነው። በዚህ ጽሁፋችን ላይ የፋይናንስ ነፃነትዎን ለመቀዳጀት እንዲችሉ ሊያስወግዷቸው የሚገቡ አንዳንድ ዋነኛ የገንዘብ ነክ ስህተቶችን ለማሳየት እንሞክራለን።

ይህንን ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ያንብቡ: Money Mistakes to Avoid

በ 20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ መወገድ ያለባቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች

1. ለማቀድ አለመቻል

የፋይናንስ ነፃነትን ለመቀዳጀት የመጀመሪያው እርምጃ የገንዘብ አወጣጥ እቅድ ማውጣት ወይም በአብዛኛው በጀት የምንለው የምንለው ነው። ገንዘባችሁን ወይም ክፍያችሁን ከማግኘታችሁ አስቀድማችሁ ገንዘባችሁን ምን ምን ላይ እንደምታውሉት እቅድ ማዘጋጀት አለባችሁ። የምታገኙትን እያንዳንዱን ሳንቲም ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችሁን ማረጋገጥ አለባችሁ። ይህ በየዕለቱ ሳይታሰቡ እየመጡ ግን ደግሞ በጊዜ ሂደት ተደማምረው ከፍተኛ መጠን ሊኖራቸው የሚችሉትን በዘፈቀደ የሚወጡ ወጪዎችን ለማስወገድ ይረዳችኋል።

2. ገንዘብን ለመቆጠብ አለመቻል

በ 20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ስትሆኑ፣ ለድንገተኛ ጉዳዮችና ለወደፊት የእርጅና ዘመን መጦሪያ እንዲሆናችሁ ገንዘብን መቆጠብ የምትጀምሩበት ተገቢው የዕድሜ ዘመናችሁ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ምርጡ መንገድ በጀት ማውጣት ነው፤ የገንዘብ ፍላጎቶቻችሁን ወረቀት ላይ በዝርዝር አስቀምጡና ከዚሁ እቅዳችሁ ዝንፍ ሳትሉ ቀጥሉ። የገንዘብ ክፍያችሁን ስታገኙ፣ ከምንም በፊት በቅድሚያ የምትቆጥቡትን ገንዘብ ቀንሳችሁ የተቀረውን ለምትፈለጉት ጉዳይ አውሉ። ከገቢያችሁ 15% ያህሉን መቆጠብ አለባችሁ።

3. ገና በወጣትነት ዕድሜ መኪና መግዛት

በ 20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆናችሁ መኪናን መግዛት መልካም ሃሳብ አይደለም። የ 20ዎቹ የዕድሜ ክልል ለወደፊቱ ህይወታችሁ መሰረቱን የምትጥሉበት ነው። መኪና ወጪ ነው፤ ለመቆጠብ አለያም ገቢ ማስገኛ ስራ ላይ ማዋል ትችሉበት የነበረውን በርካታ ገንዘብ ለመድን ዋስትና እና መኪናውን ለመንከባከብ ታውሉታላችሁ። ከዚህ በተጨማሪም፣ መኪናውን ወደሌላ ሰው በሽያጭ ለማስተላለፍ ብትፈልጉ እንኳን መኪናው ያገለገለ በመሆኑ የአላቂ ዋጋ ወይም ዲፕሪሺየሽን ከግምት የሚገባ ይሆናል። ስለሆነም በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ስትሆኑ መኪና ከመግዛት ይልቅ ገንዘባችሁን ገቢ ሊያስገኝ በሚችል ፕሮጀክት ላይ ማዋሉ የሚበጅ ይሆናል።

4. ከምታገኙት ገቢ በላይ መኖር

በ 20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ከገቢያቸው በላይ የመኖር ዝንባሌን ስለሚያሳዩ ከፍ ያለ የብድር መጠን ውስጥ ይዘፈቃሉ። ሆኖም ግን ከምታገኙት ገንዘብ ያነሰን ወጪ ብታወጡ ቀሪውን ገንዘብ ለመቆጠብ ትችላላችሁ። ችግሩ ግን ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር የመነፃፀር ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው። ከአቅማችሁ በላይ ገንዘብ በማውጣት ዕቃዎችን መግዛት አንዳች ጥቅም የለውም፣ ይልቁንም ተጨማሪ ዕዳዎች ውስጥ ይከታችኋል። ለመክፈል የሚያስችላችሁ ቁመና ላይ ሳትሆኑ መኪና አትግዙ። የግድ መግዛት አለብን ካላችሁ ደግሞ እንደአማራጭ መኪናውን ለመግዛት ቆጥቡ እንጂ ለዛ ብላችሁ ዕዳ ውስጥ አትግቡ።

በ 30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ መወገድ ያለባቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች

1. ከቆጠባችሁት ላይ ወጪ በማድረግ ዕዳን መክፈል

በ 30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች በአብዛኛው ጥቂትም ቢሆን የቆጠቡት ገንዘብ ይኖራቸዋል። ሆኖም ግን፣ ብዙዎቹ የቆጠቡትን ገንዘብ ዕዳቸውን መክፈያ የማድረግ ስህተትን ይፈጽማሉ፤ ይህ ደግሞ ቁጠባቸውን ያራቁተዋል። ይህንን ለማስወገድ ሁነኛው መንገድ ከገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች የምታገኙትን ገንዘብ ዕዳችሁን ለመክፈል መጠቀም ነው። ከዚህ በተጨማሪም፣ አላስፈላጊ ዕዳዎችን ማስወገድ ዕዳችሁን ከቆጠባችሁት ገንዘብ ላይ አውጥታችሁ እንዳትከፍሉ ያግዛችኋል። በተጨማሪም፣ ብድር ከመውሰዳችሁ በፊት ብድር የምትበደሩትን ገንዘብ እንዴት እንደምትከፍሉ እቅድ ብታዘጋጁ በጣም መልካም ይሆናል።

2. በምትገነቡት ወይም በምትገዙት ቤት ላይ በጣም ከፍ ያለ ገንዘብ ማውጣት

ለራሳችሁ በቂ የሆነ ቤትን መገንባት ወይም መግዛት በጣም መልካም ነገር ነው። ከሚያስፈልጋቹ በላይ ግዙፍ ቤት መግዛት አንዳች ጥቅም የለውም። ቤታችሁ ገቢ የሚያስገኝላችሁ ባለመሆኑ እንደ ኢንቨስትመንት ሊቆጠርም አይችልም። ስለሆነም በእሱ ላይ በጣም ከፍ ያለ ወጪን ማዉጣት ተመራጭ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ገንዘቡን ገቢ ማስገኛ ሊሆን ወደሚችል ፕሮጀክት ብታዞሩት ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። ቤታችሁ በጣም ትልቅ ከሆነ፣ እሱን አከራዩትና ሌላ አነስ ያለ ቤት ተከራዩ።

3. የወር ገቢን እንዳለ መጠቀም

ሊከሰቱ ለሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ውድቀቶች ወይም ድንገተኛ ጉዳዮች ዘወትር ዝግጁ መሆን መቻል አለባችሁ። ስራችሁን ልታጡ የምትችሉበት ክስተት ሊኖር ስለሚችልም ለዚሁ አስቀድሞ ማቀድ ያስፈልጋል። በ 30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለጡረታ ዘመናችሁ ዝግጅት እንዲሆናችሁ ኢንቨስት ማድረግ አለባችሁ። የወር ገቢያችሁን እንዳለ ወይም ሙሉ በሙሉ መጠቀምን ለማስወገድ በጀታችሁን ማቀድና በገቢያችሁ ልክ ብቻ መኖር ያስፈልጋችኋል።

4. ኢንቨስት ለማድረግ አለመቻል

ገንዘባችሁን ቀደም ብላችሁ በወጣትነት ዘመናችሁ ኢንቨስት ማደረግ መቻላችሁ በጣም መልካም ነገር ይሆናል። በ 30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ገንዘባችሁን ኢንቨስት ማድረግ ስትጀመሩ፣ ቀደም ብላችሁ ገቢ ማግኘት የምትጀምሩ ከመሆኑም ባሻገር ከመደበኛ ስራችሁ በተጨማሪ በርካታ የገቢ ምንጮች ይኖሯችኋል። ይህ ደግሞ ለጡረታ ዘመናችሁ ዝግጁ እንድትሆኑ ከማድረጉም ሌላ ተጨማሪ ስራ መስራት ሳያስፈልጋችሁ ገቢን ታገኛላችሁ። ለምሳሌ፣ በየወሩ መጨረሻ ላይ ገቢዎችን ማግኘት በምትችሉባቸው እንደ የቤት ግንባታ ቢዝነሶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትችላላችሁ።

ከቢዝነስ ወይም ንግድ ስራ ጋር በተያያዘ ሊወገዱ የሚገባቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች

ቢዝነስ ወይም የንግድ ስራ ድርጅት ካላችሁ፣ ከዚህ በታች በተመለከቱት የገንዘብ ነክ ስህተቶች እና እንዴት እንሱን ማስወገድ እንደሚቻል ግንዛቤ ሊኖራችሁ ይገባል።

1. ገንዘብን በጀት ለማድረግ አለመቻል

ከንግድ ስራችሁ በምታገኙት ገቢ እና ወጪዎች መካከል ሚዛን መጠበቅ አለባችሁ፤ ይህንንም ለማድረግ ሁነኛው መንገድ የበጀት እቅድ አዘጋጅቶ በዛው ልክ መንቀሳቀስ መቻል ነው። ኪሳራን ለማስወገድም ወጪዎቻችሁን መቼ መቀነስ እንዳለባችሁ ማወቅ አለባችሁ። ለምሳሌ፣ የሽያጭ መጠን ሊቀንስ እንደሚችል ካወቃችሁ፣ የንግድ ስራ ወይም የቢዝነሳችሁን ወጪዎች ለመቀነስ ሁሌም መንገድ ማግኘት ትችላላችሁ።

2. የንግድ ስራ ገንዘብን እና የግል ገንዘብን መደበላለቅ

የራሳችሁን የግል ገንዘብ እና የንግድ ስራ ገንዘባችሁን መለያየት አለባችሁ። ለንግድ ስራችሁ የራሱ የሆነ የሂሳብ አካውንት እንዲኖረው ማድረግ በጣም ተመራጩ ነገር ነው። ለንግድ ስራችሁ የተለየ የሂሳብ አካውንት መኖሩ የንግድ ስራውን የሂሳብ ፍሰቶች ለመቆጣጠር ይረዳችኋዋል። የንግድ ስራው ትርፍ እያስገኘ መሆኑን ለማወቅም ያግዛችኋዋል። ለምሳሌ፣ ከግል ገንዘባችሁ ላይ በርከት ያለ ገንዘብን ወደንግድ ስራችሁ የምታስገቡ ከሆነ፣ ይህን ገነዘብ በንግድ ስራው ከተገኘው ትርፍ ጋር ልታምታቱት ትችላላችሁ።

3. ዋጋን መቀነስ

ከፍተኛ የሆነ ፉክክር በሚኖርበት ጊዜ፣ በርካታ የንግድ ስራ ድርጅቶች የምርቶቻቸው እና የአገልግሎት ዋጋቸውን የመቀነስ ዝንባሌ አላቸው። ይህ በተለይ በጀማሪ አነስተኛ የንግድ ስራ ድርጅቶች ላይ የተለመደ አሰራር ነው። የዚህ የስራ ዘርፍ ደንብ እንደሚያመለክተው ግን አንድ የንግድ ድርጅት የዕቃዎቹን እና የአገልግሎቶቹን ዋጋዎች መወሰን ያለበት የንግድ ስራውን ለመስራት ያወጣቸውን ወጪዎች በሙሉ ከግምት በማስገባት ነው። ዋጋን መቀነስ ለአጭር ጊዜ ሊሰራ ይችል ይሆናል፣ ሆኖም ግን የንግድ ድርጅታችሁን ሊያዘጋችሁም ይችላል። ሆኖም ግን፣ የምርቶቻችሁን እና የአገልግሎታችሁን የመሸጫ ዋጋዎች በምትወስኑበት ጊዜ፣ ከተፎካካሪዎቻችሁ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የሆነ ዋጋን ለማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ።

4. የንግድ ስራ ማስጀመሪያ ወጪዎችን ከልክ በላይ ማውጣት

በርካታ ሰዎች የንግድ ስራዎችን ሲጀምሩና ንግዳቸው እንዴት እንደሚያድግ ሲያስቡ በጣም ተስፈኛ የመሆን ዝንባሌ ያድርባቸዋል። ይህ መልካም ነገር ቢሆንም እውነታውን መጋፈጥም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። አንድን የንግድ ስራ ወይም ቢዝነስ በትንሹ መጀመርና በዕቃዎች ወይም ምርቶችና አገልግሎቶች ፍላጎቶች ላይ በመመስረት ንግዱን እያስፋፉ መሄዱ በጣም ተመራጩ ነገር ነው። ይህ የንግድ ስራ መነሻ ወጪዎችን ከልክ በላይ ከማውጣት ያድናችኋዋል። እንደውም መልካም የሚሆነው ለንግድ ስራው ማስጀመሪያ ወይም መነሻ በጀት ማዘጋጀትና በዚህ በተዘጋጀው በጀት መሰረት መንቀሳቀስ ነው። የንግድ ስራችሁ አንዴ መሬት ረግጦ መንቀሳቀስ ከጀመረ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ልታስፋፉት ትችላላችሁ።

5. ለራሳችሁ የገንዘብ ክፍያ አለማድረግ

ብዙ ሰዎች ለንግድ ስራቸው እውን መሆን ያደረግትን ጥረት በሂሳባዊ ስሌት ከግምት ስለማያስገቡት ለራሳቸው የገንዘብ ክፍያን አይፈጽሙም። ራሳችሁን የራሳችሁ አለቃ አድርጋችሁ ማሰብና ለሰራችሁትም ስራ ክፍያ እንደሚገባችሁ ማወቅ አለባችሁ። እንደውም፣ ደሞዛችሁን በቢዝነስ ወይም በንግድ ስራው የወጪዎች ዝርዝር ውስጥ ማካተት ይገባችኋዋል። ይህን ማድረጋችሁ ከንግድ ስራው ገንዘብ ከመንካት ይልቅ ለግል ወጪዎቻችሁ መሸፈኛ በመሆን ይረዳችኋዋል። ለራሳችሁ ከሚገባችሁ በታች ክፍያን መፈጸም የለባችሁም፤ ለሌላ ሠራተኛ በምትከፍሉት የገንዘብ መጠን ልክ ለራሳችሁም መክፈል ይገባል።

6. በቂ የሆነ የስራ ማስኬጃ ካፒታል አለመኖር

የስራ ማስኬጃ ካፒታል አለመኖር በብዙ አነስተኛ ቢዝነሶች ላይ የሚታይ የተለመደ ችግር ነው። አንድን የቢዝነስ ስራ ስትጀምሩ፣ ቢያንስ ለ 6 ወራት የሚሆን በቂ የስራ ማስኬጃ ካፒታል ቢኖራችሁ በጣም ተመራጭ ይሆናል። ይህ መሆኑ የቢዝነሳችሁን ወጪዎች በዘላቂነት ለመሸፈን ገንዝብ ከመበደር ያድናችኋዋል። በእርግጥ ለቢዝነስ ስራ መበደር ኃጢያት አይደለም – አብዛኛውን ጊዜ መጠነኛ የሆነ አደጋ ወይም ሪስክ ከማስከተላቸው በቀር።

መወገድ ስላለባቸው የገንዘብ ነክ ስህተቶች ማጠቃለያ ነጥቦች

በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ነፃነታችሁን በእጃችሁ ለማድረግ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ገንዘብ ነክ ስህተቶች ማስወገድ ይገባል። ይህን ለማድረግ ሁነኛው መንገድ ደግሞ ወጪዎቻችሁንና ቁጠባችሁን በበጀት መምራት ነው። በጀታችሁን አንዴ በአግባቡ ካዘጋጃችሁ በእሱና በእሱ ብቻ መመራት አለባችሁ። ይህን ማድረጉ በየጊዜው ያለእቅድ የሚመጡ ወጪዎችን ለማስወገድ ያስችላል። በበጀት ውስጥ የሌሉ ወይም ያልገቡ ወጪዎች ትናንሽ ይምሰሉ እንጂ ሲደማመሩ ከፍተኛ ወጪዎች እንደሚሆኑ መዘንጋት የለባችሁም።