ዛሬውኑ መወገድ የሚገባቸውና ወጣቶች የሚፈጽሟቸው 6 ገንዘብ ነክ ስህተቶች

ትርጉሞች:
en_USsw

የፎርብስ የዓለማችን ባለጸጎች ዝርዝር እንደሚያመለክተው፣ በዓለማችን እጅጉን ባለጸጋ የሆኑት ሰዎች ኩባንያዎቻቸውን የመሰረቱት ዕድሜያቸው ገና በአስራዎቹ ውስጥ እያለ ነው። እጅግ ባለጸጋ አሜሪካዊያን መካከል እንደ ማርክ ኩባን፣ ቢል ጌትስ እና ማይክል ዴል ያሉት ሚልየነርና ቢሊየነር መሆን የጀመሩት ገና የ 20 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ እንኳን ሳይደርሱ ነው። ይኽ ደግሞ የሚያሳየው የጉርምስና ዘመን ለአንድ ሰው ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ነው። አሳዛኙ ጉዳይ ግን፣ እጅግ የበዙ ወጣቶች የጉርምስና ዘመናቸውን በጣም በርካታ ስህተቶችን በመፈጸም የሚያባክኑት መሆኑ ነው። በዚህ ጽሁፍም፣ ሊወገዱ የሚገቡና ወጣቶች የሚፈጽሟቸውን በጣም የተለመዱ የገንዘብ ነክ ስህተቶችን ለማየት እንሞክራለን።

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: የተሳሳተው መንገድ

ብዙ ሰዎች የኮሌጅ ትምህርታቸውን የሚጀምሩት በጉርምስና ዘመናቸው ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን፣ እነዚህ ወጣቶች የበዙ ስህተቶችን የሚሠሩበት የህይወት ደረጃም ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ወጣቶች በስራ ገበያው ውስጥ በጣም ለገበያ የማይበቁ ኮርሶችን በኮሌጅ ቆይታቸው ይወስዳሉ። ይኽ በበርካታ አገራት የሚታይ እውነታ ሲሆን የስራ ገበያው ያን ያህልም አይፈልጋቸውም ከተባሉትና ወጣቶችም የሚወስዷቸው ኮርሶች መካከል እነሱን መውሰዱ የሚመከር አይደለም የተባሉት እንደ ፋሽን ዲዛይን፣ ታሪክ፣ የቤተ-መጻህፍት ሳይንስ እና ድራማ የመሳሰሉትን ይጨምራሉ።

እንደዚህ አይነት ኮርሶችን መውሰድ ብዙውን ጊዜ የማይመከሩባቸው ሶስት ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ፣ ኮርሶቹ በስራ ገበያ ውስጥ ብዙ ፍላጎት የላቸውም። ሁለተኛ፣ እነዚህ ኮርሶች ተማሪዎች በወሰዷቸው ኮርሶች ስራ ካላገኙ ለሌሎች ስራዎች እንዲያመለክቱ የሚያስችሏቸውን እውነተኛ ክህሎቶችን አያጎናጽፏቸውም። ሶስተኛ፣ ኮርሶቹ በጣም ጥሩ ክፍያ የሚያስገኙ አይነት አይደሉም። ለምሳሌ የአሜሪካኖቹን ተሞክሮ ብናይ እንኳ፣ አንድ የቤተ መፃህፍት ሳይንስ የተማረ ባለሞያ በየዓመቱ ከ 40,000 ዶላር ያነሰ ገቢ ያገኛል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ የቤተ-መጻህፍት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነው። ይህ ደግሞ የቤተ-መጻህፍት ባለሙያዎችን የሚፈልጉ ኩባንያዎች ከፍላጎት የበለጠ አቅርቦት አላቸው ማለት ነው።

የተሳሳተ መንገድ መምረጥን እንዴት ማስወገድ እንደምንችል. ይኽን የወጣቶች የተሳሳተ መንገድ የመምረጥ ስህተትን ለማስወገድ የሚከተሉትን ተግባራዊ እንድታደርጉ እንመክራለን:

  • በወደፊቱ ማለትም በመጪዎቹ ጊዜያት ስለሚኖሩት ስራዎች ወይም የስራ ዕድሎች መረጃዎችን ለማግኘት ባለሞያዎችን አማክሩ፤
  • ዙሪያችሁን ቃኙና ወደፊት ሊሰሩ ወይም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን ለማግኘት ሞክሩ፤
  • አንድን የትምህርት ኮርስ ከመወስዳችሁ አስቀድሞ ኢንድስትሪው በመጪዎቹ ጊዜያት ሊኖረው ስለሚችለው ዕድል በደንብ አስቡ።

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: የጀመሩትን ትምህርት ማቋረጥ/መተው

ብዙ ታዳጊዎች ወይም ወጣቶች ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ ይታወቃል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካቋረጡ ሰዎች ይልቅ ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚወጡ ሰዎች የበለጠ ገቢ ያገኛሉ፤ ለእዚህ ደግሞ በምክንያትነት የተጠቀሰው አብዛኛው ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈልባቸው ስራዎች የኮሌጅ ትምህርትን ያጠናቀቁ ሰዎችን መፈለጋቸው ነው። ይኽን ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰሩ ጥናቶችን ፈልገን ባናገኝም፣ አንድ አሜሪካን አገር የተደረገ ጥናት የደረሰበትን እውነትን ግን እንደማሳያ ማቅረብ እንችላለን። በመሆኑም፣ እነዚህ ጥናቶች እንዳረጋገጡት የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሰዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ካላቸው ሰዎች የ 17,000 ዶላር ብልጫ ያለው ክፍያ ያገኛሉ። ይኽ በእርግጥም ትልቅ ልይነት መኖሩን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የባችለር ዲግሪ ማለትም የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሰዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ከሌላቸው የበለጠ ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኙም ተረጋግጧል።

ስለዚህ፣ ከትምህርት ቤት ለማቋረጥ የምታስቡ ወጣቶች ከሆናችሁ፣ በጉዳዩ ላይ አስቀድማችሁ በጥልቅ እንድታስቡበት ምክራችንን እንሰጣለን። በቀሪው ህይወታችሁ ልትጸጸቱበት የምትችሉበት ስህተት መሆኑ ደግሞ የምትወስዱትን ጥንቃቄ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: የንግድ ስራን ወይም ቢዝነስን አለመጀመር

ንግድ ለሁሉም ሰው የሚሆን የስራ ዘርፍ አይደለም። ይህም ሰዎች ሁሉ ስራ ፈጣሪ ሊሆኑና ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም ማለት ነው። ስኬታማ የንግድ ሰው መሆን ወይም አለመሆናችሁን ለማወቅ በጣም ጥሩውና ምርጡ ጊዜ የወጣትነት ዕድሜያችሁ ነው። ከላይ እንደተገለፀው፣ ዓለማችን በወጣትነት ዘመናቸው ኩባንያቸውን የጀመሩ ብዙ ቢሊየነሮችን እና ሚሊየነሮችን ያቀፈች ናት።

የንግድ ስራን ወይም ቢዝነስን በወጣትነት ዘመናችሁ መጀመርን የግድ እንድትሉ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንደሚከተሉት መግለጽ ይቻላል:

  • በወጣትነታችሁ ምክንያት የበዙ ኃላፊነቶች የሉባችሁም፤
  • ለመውደቅ ነፃነት አላችሁ – ለመነሳት ጊዜ። ብትወድቁ ወይም ስኬታማ ባትሆኑ እንኳን ወጣትነት ሁል ጊዜ ወደፊት እንድታዩ እና ጥሩ ስራ እንድታገኙ ዕድል ይሰጣችኋል፤
  • ወጣትነት የንግድ ስራችሁን ለማስኬድ ወይም ለማከናወን የምትችሉበትን ብዙ ነፃ ጊዜ ይሰጣችኋል፤
  • ወጣትነት በህይወታችሁ የመጀመሪያ ዘመናት ላይ ለጡረታ ዘመናችሁ በጊዜ ገንዘብ መቆጠብ እንድትጀምሩ ያስችላችኋል።

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: ገንዘብ አባካኝነት

ዩቲዩብ፣ Snapchat፣ Instagram እና TikTok የፍጆታ ባህል እንዲፈጠር አግዘዋል። እነዚህ የማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ወይም ፕላትፎርሞች በገጾቻቸው ላይ የሰዎችን ኑሮ ወይም አኗኗር ፍጹም የተሟላ እንደሆነ አድርገው ያሳያሉ። በዚህ ምክንያት ኩባንያዎች በገበያ ዘመቻቸው ታዳጊዎችና ወጣቶችን ኢላማ ማድረግ ከጀመሩ ከራርመዋል። ለምሳሌ፣ እንደ አፕል እና ማይክሮሶፍት ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ በተለይ በእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን ቀጥረው በማሰራት ላይ ይገኛሉ።

ይህ ሁሉ በመሆኑም ደግሞ በቁጥር እጅግ የበዙ እ.ኤ.አ ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ጊዜያት የተወለዱና ፈረንጆቹ ሚሊኔያልስ የሚል መለያ ስም የተሰጣቸው ሰዎች እና ታዳጊዎች ዋነኛ ትኩረታቸው በፍጆታ ባህል ላይ እንዲጠመድ ሆኗል። እነዚህ ወጣቶች የቅርብ ጊዜውን ማለትም የመጨረሻ ዘመናዊ የሆነውን አይፎን እና የማይክሮሶፍት ሰርፈስ ዲቫይስ ወይም መሳሪያ መግዛት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ በተራው ወጣቶቹ መጠኑ ከፍ እያለ በሚሄድ የገንዘብ የእዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ አድርጓል። እንደ አንድ መፍትሄም፣ ጥሩ በሆነ የበጀት እቅድ መመራት ይህንን ገንዘብ ነክ ስህተት ለመከላከል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖ እራሳቸውን ወደ ዕዳ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች በህይወት ውስጥ እምብዛም ስኬታማ አይደሉም። ምክንያቱም ከገቢያቸው አብዛኛው ዕዳቸውን ለመክፈል ስለሚውል ነው። ዕዳ ውስጥ ስትዘፈቁ የሱ ባሪያ እንደምትሆኑ ሁሌም ልብ ልትሉ ይገባል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ሊያስወግዷቸው ከሚገቡ የተለመዱ ነገሮች መካከል ደግሞ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ:

  • አዳዲስ አይፎን እና የአፕል ሰአቶችን/አፕል ዋችስ የመሳሰሉ ምርቶችን፤
  • ጉቺ እና ፕራዳን የመሳሰሉ ውድ ውድ የሆኑ ፋሽኖችን፤
  • ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ሬስቶራንቶችን።

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: ለጡረታ ዘመን የሚሆን ገንዘብን አለመቆጠብ

ብዙ ወጣቶች ከሚፈጽሟቸው የተለመዱ ስህተቶች መካከል አንዱ ስለወደፊቱ የጡረታ ዘመናቸው አለማሰባቸው ነው። የጡረታ ዘመንን እጅግ በጣም የራቀ አድርገው ያስቡታል። ይኽ ደግሞ ወደፊት ሊፀፀቱበት የሚችሉት ግዙፍ ስህተት ነው። አሁን ላይ ዕድሜያችሁ 20 አመት ከሆነ ስለጡረታ ዘመናችሁ ማሰብ መጀመራችሁ በጣም ብልህነት የተሞላበት አድራጎት ይሆናል። ለምሳሌ፣ ዕድሜያችሁ 15 አመት ሲሞላ በየወሩ 100 ብር መቆጠብ ብትጀምሩ፣ የባንክ ወለድን ሳይጨምር ዕድሜያችሁ 60 አመት ሲሞላ 54000.00 ብር የቆጠባችሁት ይኖራችኋል ማለት ነው።

ተመሳሳይ የገንዘብ መጠንን ዕድሜያችሁ 30 አመት ሲሞላ መቆጠብ ብትጀምሩ፣ 60 አመት ሲሞላችሁ የቆጠባችሁት የገንዘብ መጠን ብር 36000.00 ይሆናል። ጡረታ ከወጣችሁም በኋላ ከ 15 አመት በላይ በህይወት ልትቆዩ እንደምትችሉ ልብ ማለት አለባችሁ። እነዚህን ሁሉ ስናስብ ነው እንግዲህ ለጡረታ ዘመናችሁ የሚሆን ገንዘብን ገና ወጣቶች ሆናችሁ መቆጠብ መጀመር አለባችሁ ብለን ምክራችንን የምለግሰው። ይኽንን ደግሞ የትርፍ ሰአት ስራዎችን እንዲሁም ግራፊክ ዲዛይን እና ድረ ገጾችን ዲዛይን ያሉ አጫጭር ስራዎችን ጎን ለጎን በመስራት ልትፈጽሙት ትችላላችሁ።

የጉርምስና ወይም የወጣትነት ጊዜ አስደሳችም አስቸጋሪም የህይወታችን ወቅት ነው። ምርጥ ምርጥ የሆኑ ጓደኞችን የምታፈሩበት ጊዜም ነው – የዛን ዘመን ያወቅኳቸው መቼም ከልቤ የማይወጡና አሁን ድረስም የማገኛቸውና የማወራቸው ጓደኞች አሉኝ። የወጣትነት ምርጥም መጥፎም ነገሮችን የሚያሳየንና የምናገኝበት የህይወታችን አንድ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ምርጥ የህይወት ዘመን ጓደኞችን እንዲሁም ልብን ክፉኛ በሀዘን ሰባሪዎችንም የምናገኝበት ነው። ሶፊያ ቡሽ (ታዋቂ አሜሪካዊት የፊልም አዘጋጀና ተዋናይ እንዲሁም አክቲቪስት)

ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ገንዘብ ነክ ስህተቶች: አዳዲስ ክህሎቶችን አለመማር

የጉርምስና ዘመናችሁ የሚለግሳችሁ ትልቁ ሀብት ጊዜ ነው። ስራችሁን ወደፊት ለማራመድ ወይም ለማሳደግ ልትጠቀሙበት የምትችሉት መጠኑ የበዛ ነጻ ጊዜ አላችሁ። ስለዚህ፣ ኮሌጅ ውስጥ እያላችሁም እንኳ አዳዲስ ክህሎቶችን መማር መጀመር እንዳለባችሁ እንመክራለን። እንደ እድል ሆኖ ደግሞ አዳዲስ ክህሎቶችን ለመማር የሚረዷችሁ በርካታ መድረኮች ወይም ፕላትፎርሞች አሉ። እነዚህ ፕላትፎርሞችም ከዚህ በታች በእንግሊዘኛ የዘረዘርናቸውን ያካትታሉ:

  • Udacity
  • Coursera
  • Skillshare
  • Khan University
  • EDX

ማጠቃለያ

የጉርምስና ወቅት ለእያንዳንዱ ሰው በጣም በጣም አስፈላጊ የሆነው ጊዜ ነው። ለወጣቶች የህይወታቸው መሠረት የሚጣልበት ወሳኝ የጊዜና የህይወት ምዕራፍ ነው። ወጣቶች ስህተት እንዲሰሩ የሚፈቀድበት ብቸኛ ወቅት ይኼ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። ስለዚህ፣ እነዚህን ስህተቶች በማስወገድ እና በራሳችሁ ላይ ኢንቨስት በማድረግ በታዳጊነት ዕድሜያችሁ ለመጪውና ለረጅሙ የህይወታችሁ ምዕራፍ ጥሩ መሰረት ማዘጋጀትም ትችላላችሁ። ምናልባት አሁን በጉርምስና ዘመናችሁ የማታውቁት ነገር ቢኖር ከወጣትነታችሁ ይልቅ በኋለኛው ዘመናችሁ መዝናናት የበለጠ አስደሳች መሆኑን ነው።