እኛ ሁልጊዜ የምንመክረው አንድ የተለመደ የህይወት ህግ ወይም መመሪያ አለን፤ ይኸውም፣ በመደበኛነት ተቀጥራችሁ በምትሰሩት ስራ በወር የቱንም ያህል ገቢ ብታገኙም አንድ የገቢ ምንጭ ሊኖራችሁ ፈጽሞ አይገባም። ይኽን አጥብቀን የምንመክረው ያለምክንያት አይደለም። መደበኛ ስራችሁን የቱንም ያህል የገዘፈ ስምና ሀብት ያለው ኩባንያ ብትሰሩ መጥፎ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ኩባንያው በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከስራ ገበታችሁ ላይ ሊያሰናብታችሁ ይችላል። በኪሳራም ምክንያት ጭራሹኑ ሊዘጋ ይችላል። ባለፉት አስር እና ሃያ አመታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትላልቅ ኩባንያዎች በኪሳራ ምክንያት ከጨዋታ ውጪ እንደሆኑ ለማወቅ ጥቂት መረጃዎችን ብቻ ማገላበጥ ይበቃል።
የብዙ የገቢ ምንጮች መኖር የማይቀረው መጥፎ ነገር ቢከሰት እንኳን መክላከያ ጋሻ እንዲኖራችሁ ያደርጋል። በዚህ ጽሑፍም፣ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁን ወደ ዋናው መሸጋገሪያ ድልድይ እንዲሆን እንዴት መጠቀም እንደምትችሉ የሚያመለክቱ ምርጥ መላዎችን እንቃኛለን።
Contents
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ (Side Gig) ምንድን ነው?
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ (ፈረንጆቹ Side Gig ወይም side Hustle እያሉ ይጠሩታል) ገቢ ከምታገኙበት የሙሉ ጊዜ ስራችሁ በተጨማሪ ወይም ጎን ለጎን የምትሰሩት ማንኛውም ስራ ማለት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አማካይ ሳምንታዊ የስራ ጊዜ መጠን 40 ሰዓት ያህል በመሆኑ ብዙ ሰዎች አንድ ነገር ለማድረግ በእጃቸው ብዙ ጊዜ አላቸው። በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ ሰዎች ከአንድ በላይ ስራዎችን የመስራት ዕድል ማግኘት እየጀመሩ ነው። ይኽ ጅማሮ ገና ብዙ የሚቀረውና ሀገሪቱም ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ችግር አኳያ በርካታ ቀጣሪ ኩባንያዎች ባይኖሩም ወደፊት ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ጉዳዩ ባህል እየሆነ ሊመጣ እንደሚችል ግን ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ከዚህ አኳያ የአሜሪካኖቹን ተሞክሮ ለአብነት ያህል ብንመለከት መልካም ነው። የአሜሪካየህዝብ ነክ ጉዳዮች ቢሮ (Census Bureau) የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከ 7.5 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ሌሎች ከአንድ በላይ ስራዎችን በየዕለቱ ይሰራሉ። አሜሪካኖቹ ከአንድ በላይ ስራዎች የሚሰሩበት ምክንያቶች ደግሞ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል:
- የበለጠ ገንዘብ ለማግኘት፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሁለት ስራዎችን የሚሰሩት አሁን የሚያገኙትን ደሞዝ መተን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ነው።
- ወደፊት ለሚያቋቁሙት ኩባንያ ወይም የግል ቢዝነስ እንደመነሻ እንዲሆናቸው ነው፤ በርካታ ሰዎች የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራቸውን የራሳቸውን የግል ቢዝነስ ስራ መነሻ ገንዘብ አድርገው ይጠቀሙበታል።
- ለጊዜ መግደያነት፤ በየዕለቱ ለጥቂት ሰአታት ብቻ የሚሰሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራቸውን በጊዜ ማሳለፊያነት ይጠቀሙበታል።
- የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያነት (እንደ ሆቢ)፤ ከላይ የተጠቀሰው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አንዳንድ አሜሪካዊያን የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራቸውን በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያነት እንደሚጠቀሙበት ነው።
- የስራ ልምድን ለማሳደግ፤ አሜሪካ ውስጥ ያሉ ብዙ ቀጣሪ ድርጅቶች በድርጅታቸው ውስጥ መቅጠር የሚፈልጉት የስራ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ነው። በዚህም ምክንያት፣ ሰዎች የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራን እንደ ልምድ ማካበቻ በመጠቀም የስራ ልምድ መግለጫቸውን (resume) ያጠናክሩበታል።
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ ምሳሌዎች በጥቂቱ
እንደ ልማድ ሆኖ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው ጥያቄ ምን ምን ስራዎችን እንደ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ ምሳሌዎች አድርገን ማንሳት እንችላለን የሚል ነው። ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እውነታ አኳያ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው እዚህ ላይ ማንሳት የምንችለው። አንድ እውነት ግን ሊታወቅ ይገባል፤ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ እናንተን የሚያስደስትና የሚስብ አይነት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ ሳይፈጅባችሁ ልትጀምሯቸው የምትችሏቸው የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ ምሳሌዎችን በጥቂቱ ለመጥቀስ፡
- ግራፊክስ ዲዛይን – ይህ እንደ በራሪ ወረቀቶች፣ አርማዎች እና መጽሄቶች ያሉ ነገሮችን ዲዛይኖች መስራትን ያካትታል፤
- የግል ድርጅቶች ጥበቃ ወይም ጽዳት ስራ፤ – ይህ በአውትሶርሲንግ አማካኝነት የሚሰሩ ስራዎችን ያካትታል፤
- በግል ሆስፒታሎች እና በክሊኒኮች ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት ስራ፤
- የከተማ ውስጥ የታክሲ ስራ – እንደ ፈረስ፣ ራይድ እና ሌሎች ፕላትፎርሞችን በመጠቀም ይህን አገልግሎት በመስጠት ገቢ ማግኘት ትችላላችሁ።
- አካባቢያዊ አነስተኛ የንግድ ስራዎች – በየአካባቢያችሁ በተለይ ባዶ ስፍራ የምታገኙ ከሆነ ወይም የሰው ቤት ተከራይታችሁ የሻይና ቡና እንዲሁም የፈጣን ምግብ አገልግሎት በመስጠት ገቢ ማግኘት ትችላላችሁ።
- በበይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት ላይ ጽሁፎችን ማውጣት/ቪዲዮዎችን መጫን – ይኽ ጽሁፋችሁን ወይም የቀረጻችሁትን ቪዲዮ በቀጥታ ማለትም ኦንላይን በመጫን ገቢ ልታገኙበት የምትችሉበት ነው።
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎች ባህርያት ምንድን ናቸው?
ሁሉም የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎች ተመሳሳይ አይደሉም፤ የሚጠይቁት ጥረትና ልፋትም እንዲሁ የተለያየ ነው። የሆኖ ሆኖ ግን ጥሩ የሚባል የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ በርከት ያሉ ባህሪያት/መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡
- እየወደዳችኋቸው ይምትሰሯቸው ስራዎች ሊሆኑ ይገባል።
- ስራዎቹ ገንዘብ የሚያመጡ ወይም ገቢ የሚያስገኙ ሊሆኑ ይገባል።
- በመደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራችሁ ላይ ጣልቃ ሊገቡ አይገባም።
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎቻችሁን እንዴት ወደ የሙሉ ጊዜ የንግድ ወይም ቢዝነስ ስራ ማሸጋገር እንደሚቻል
እስካሁን የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎች የሚባሉት ምን እንደሆኑ እንዲሁም ምሳሌዎችንም ተመልክታችኋል። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እነዚህን ስራዎች እንዴት ወደ የሙሉ ሰአት የንግድ ወይም ቢዝነስ ስራ ማሸጋገር እንደምትችሉ እናሳያችኋለን። ታሪክ እንደሚያመለክተን፣ የዓለማችን ታላላቅ የሚባሉት ግዙፍ ኩባንያዎች አጀማመራቸው እንደ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ ሆነው ነበር። እንደ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ Houzz፣ Groupon፣ WeWork፣ እና Udemy ያሉ ትላልቅ ስሞችን ከብዙዎቹ መካከል መጥቀስ እንችላለን።
በምትሰሩት ስራ ላይ ጥሩና አሪፍ ሁኑ
በምትሰሩት ስራ ላይ ጥሩና አሪፍ መሆን ይገባችኋል። የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁ በኦንላይን ግንኙነት ስልጠና መስጠት ከሆነ፣ እጅግ በጣም ጥሩ የሆኑ ኮርሶችን ለመቅረጽ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባችሁ። ኮርሶቹ ለየት ያሉና ስትቀርጿቸውም ለተማሪዎቻችሁ እሴት ወይም ቫልዩ የሚጨምሩ አድርጋችሁ ሊሆን ይገባል።
መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራችሁን ከመተዋችሁ በፊት የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁ ውጤት ማግኝት አለባችሁ
የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎችን በሚሰሩ ብዙ ሰዎች የምናየው አንድ የተለመደ ስህተት የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራቸው ውጤት ማስገኘቱን ሳያረጋግጡ መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራቸውን መተዋቸው ነው። ሁሌም የምንመክረው ግን ሰዎች መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራቸውን መተው ያለባቸው የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራቸው ውጤት ማስገኘቱን ካረጋገጡ በኋላ ብቻ መሆን እንዳለበት ነው። ለምሳሌ፣ የዩቲዩብ ቻነል ካላችሁ፣ መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራችሁን መተው የሚኖርባችሁ በቻነሉ በምትሰሩት ስራ ጥሩ ገንዘብ እየሰራችሁ መሆኑን ስታረጋግጡ ብቻ ነው።
መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራችሁን ከመተዋችሁ በፊት ረዳት ቅጠሩ
አንዳንድ ጊዜ እንደውም መደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራችሁን ሁሉ መተው ላያስፈልጋችሁ ይችላል። የምታከናውኗቸው አንዳንዶቹ ስራዎች በረዳት ሰራተኛ ሊሰሩ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አካባቢያዊ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን እንደ ጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ የምትሰሩ ከሆነ፣ ያለብዙ ጥረት ረዳት በመቅጠር ልታሰሩ ትችላላችሁ። የእናንተ ስራ የረዳቱን ስራ መምራትና አስፈላጊ ለስራው ግብአቶችን ማቅረብ ብቻ ሊሆን ይችላል።
በቂ መጠን ያለው ገንዘብ አስቀድሞ በጎን ማኖር
የመደበኛ የሙሉ ጊዜ ስራ መኖር ጠቃሚነቱ ተገማች የሆነ ገቢ ማስገኘቱ ነው። በየወሩ መጨረሻ ቀናት ላይ ደሞዝ እንደምታገኙ እርግጠኞች ናችሁ። ከተቀጣሪነት ወደየቢዝንሰ ወይም የንግድ ስራ ባለቤትነት ስትሸጋገሩ፣ የህይወትን ነባራዊ እውነታዎች ልትረዱ ወይም ልትገነዘቡ ይገባል። የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁ እድገት ማሳየት ከመጀመሩ በፊት የምታገኙት የገቢ መጠን ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ፣ ሊከሰቱ የሚችሉትን ማናቸውንም አደናቃፊ ችግሮች ለመጋፈጥና ለመቋቋም የሚያስችላችሁን በቂ ገንዘብ አስቀድማችሁ በጎን ማስቀመጥ አለባችሁ።
ማሳደግ
በስተመጨረሻም፣ ትኩረታችሁን ሁሉ አዲሱ ቢዝነሳችሁ እና እሱንም እንዴት ማሳደግ እንደምትችሉ ማውጠንጠንና መተግበር ላይ ማሳረፍ አለባችሁ። ይኽም ቢዝነሳችሁ ወይም የንግድ ስራችሁ ላይ የምታሳልፉትን የጊዜ መጠን በሁለትና በሶስት እጥፈ መጨመር ያስፈልጋችኋል ማለት ነው። ቢዝነሳችሁን ለማሳደግ ድጋፍ የሚያደርጉላችሁን ሰራተኞች ቅጥርም ማፋጠን አለባችሁ።
ልንወስዳቸው የሚገቡ መሰረታዊ ትምህርቶች/ግንዛቤዎች
ጥሩ የሆነ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ብድሮቻችሁን ለመክፈል እና የዕለት ተዕለት ወጪዎቻችሁን ለመሸፈን የሚረዳችሁ ገንዘብ ታገኙበታላችሁ። ከመደበኛ ስራቸው የሚያገኙትን ክፍያ አምስት ሳንቲም ሳይነኩ በጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎች የሚያገኙትን ገቢ ብቻ የሚጠቀሙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ልብ ልትሉ ይገባል። የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁ እያደገ ሲመጣ ስራውን ማስፋፋት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይኽን ደግሞ ማድረግ የምትችሉት የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራችሁ ትልቅ ድርጅት ሊሆን ይችላል የሚል ፅኑ እምነት በራሳችሁ ላይ ካሳደራችሁ ነው። እዚህ ላይ ቁርጠኛ የሆነ ውሳኔ ካላችሁ፣ ለሽግግሩ አስፈላጊ ናቸው ብለን የዘረዘርናቸውን ስልቶች ወይም ስትራተጂዎች መከተል አለባችሁ።