አጠር ባለ ጊዜ ገንዘብ በፍጥነት የማግኛ መንገዶች (How to Get Money Fast)

ትርጉሞች:
en_US

አንዳንድ ጊዜ ራሳችሁን በአስቸኳይ ገንዘብ በምትፈልጉበት ሁኔታ ውስጥ ልታገኙት ትችላላችሁ። ድንገተኛ አደጋ ወይም ሁኔታ ተከስቶ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ራሳችሁን ከዚህ ሁኔታ ለማውጣትና እርምጃ ለመውሰድ ስትፈልጉ ደግሞ እየቆጠባችሁ ያጠራቀማችሁት የተወሰነ ገንዘብ ያህል እንኳን የላችሁም። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ግን ራሳችሁን በፍጹም ጭንቀት ውስጥ መክተት የለባችሁም። በጣም በአጠረ ጊዜ ውስጥ ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደምትችሉ የሚያሳይዋችሁ አንዳንድ ፈጣን መፍትሄዎች አሉ። እኛም በዚህ ጽሁፋችን በአጠረ ጊዜ ውስጥ ገንዘብ በፍጥነት ለማግኘት የሚያስችሏችሁን አንዳንድ ስልቶች እናመለክታችኋለን።

አጠር ባለ ጊዜ ገንዘብ የማግኛ መንገዶች

  • ከጓደኞች ወይም ከቤተሰብ መበደር።
  • እንደ መኪና ያሉ አንዳንድ ንብረቶች ባለቤት ከሆናችሁ የባለቤትነት ደብተራችሁን ወይም ማስረጃችሁን አስይዛችሁ ብድር ማግኘት ትችላላችሁ። መያዣ ይዘው የሚያበድሩ መደብሮችም ብድር ሊሰጧችሁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አማራጮች በረጅም ጊዜ ውስጥ ውድ ሊሆኑ ይችላሉ።
  • እንደ አገልግሎት አቅራቢ፣ ጽዳት፣ ወይም የልጆች ጥበቃ እንክብካቤ ያሉ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁና ክፍያውንም በቶሎ የሚፈጸምባቸው ስራዎችን መስራት።
  • አንዳንድ ንብረቶቻችሁን በኦንላይን መሸጥ።

ከጓደኛ ገንዘብ መበደር

በአስቸኳይ ገንዘብ ካስፈለጋችሁ ከምታምኑት ጓደኛችሁ የተወሰነ መበደር ትችላለችሁ። ከጓደኛችሁ ብድር ለማግኘት ታማኝ ወይም እምነት የሚጣልባችሁ መሆን አለባችሁ። ብድሩን ለመክፈል የሚያስችል ስልት እንዳላችሁ በቅድሚያ ማረጋገጥ ያለባችሁ ከመሆኑም ባሻገር የብድሩን አወሳሰድ እና አመላለስ በተመለከተ በሚኖሩት ግዴታና ደንቦች ላይ በጽሁፍ ስምምነት ማድረግ ትችላላችሁ። ለጓደኛችሁ ታማኝ ሁኑ፤ ገንዘቡን በአስቸኳይ ለምን እንዳስፈለጋችሁ ምክንያቱን ብታሳውቋቸው መልካም ነው።

ልጆችን የመጠበቅ እና የመንከባከብ ስራ መስራት

ልጆችን የምትወዱ ከሆነ፣ የልጆች ጥበቃና እንክብካቤ የመሰለ የጎንዮሽ ስራ መፍጠር ትችላለሁ፤ ለዚህም አገልግሎታችሁ በጥሩ ስምምነት አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎችን እንደምታገኙ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። ለአገልግሎቱ ብዙ መድከም አያስፈልጋችሁም። በአካባቢያችሁ ካሉ ወላጆች ጋር ቀረባችሁ ሃሳባችሁን ንገሯቸው፤ እነሱ አገልግሎቱን ባይፈልጉም ለጓደኞቻቸው ወይም ለወዳጆቻቸው ይኽን አገልግሎት እንደምትሰጡ ሊነግሩላችሁ ይችላሉ። በማህበራዊ ሜዲያ ገጻችሁም ላይ ከመደበኛ ስራችሁ ሌላ የልጆች ጥበቃ እና እንክብካቤ አገልግሎትን እንደምትሰጡ ማሳወቅ ትችላላችሁ፤ ይኽን በማድረግም የገጻችሁ ተከታዮች አገልግሎቱን በሚፈልጉበት ወቅት ወደ እናንተ የሚመጡበትን አጋጣሚም ማመቻቸት ትችላላችሁ።

በበይነ መረብ ወይም በኢንተርኔት ግንኙነት በኦንላይን በሚደረጉ ጥናቶች ላይ መሳተፍ

ብዙ ኩባንያዎች በኦንላይን ግንኙነት አማካኝነት ጥናት እና ምርምር በማካሄድ ስለምርታቸው ወይም አገልግሎታቸው የሰዎችን ግብረ-መልስ ወይም አስተያየት ለማግኘት ይፈልጋሉ።ጥናት አድራጊ ኩባንያዎቹ እናንተ አንድ የሆነ አይነት ምርትን ስለመጠቀም ወይም ደግሞ ስለ አንድ የተወሰን ጥናት ወይም ምርምር ያላችሁን ተሞክሮ (ልምድ) ምላሽ እንድትሰጧቸው ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን ሊጠይቋችሁ ይችላሉ። በኦንላይን የዳሰሳ ጥናት ፕላትፎርሞች ወይም መድረኮች ላይ በመመዝገብ በጥናቶች ላይ መሳተፍ መጀመር ትችላላችሁ። በአብዛኛው የዳሰሳ ጥናትን ሞልቶ ለማጠናቀቅ 30 ደቂቃ ያህል ይወስዳል፤ ይኽን አድርጋችሁ ስትትጨርሱም መጠኑ አነስ ያለ ሊሆን ቢችልም የገንዘብ ክፍያ ይደረግላኋል። የሜሪካን አገርን ልምድ ብንወስድ ለአብነት ያህል፣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ለሚሳተፍ አንድ ሰው የሚሰጠው ክፍያ በአማካይ እስከ 5 ዶላር (በኢትዮጵያ የወቅቱ ምንዛሪ እስከ 250 ብር) የሚደርስ ሲሆን ክፍያዎች የሚፈጸሙባቸውም ዘዴዎች PayPal፣ የስጦታ ካርዶች፣ ቼክ ወዘተ ያካትታሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ምርጥ የኦንላይን ዳሰሳ ድረ-ገጾች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

የግምገማ አስተያየቶቻችሁን በኦንላይን ማቅረብ

በቤታችሁ ሆናችሁ ምርቶችን መሞከር እና መገምገም በዚህም ደግሞ ጥቂት ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ። ከእናንተ የሚጠበቀው ስለ አንድ አገልግሎት ወይም ምርት አስተያየት መስጠት ብቻ ነው። እንደ UserTesting.com፣ ProductReportCard፣ Opinion Outpost እና Daily Goodie Box ባሉ መድረኮች ወይም ፕላትፎርሞች ላይ በመመዝገብና ምርትን በመገምገም እና አስተያየት በመስጠት ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ። አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ለመገምገም 25 ደቂቃ ብቻ ሊወስድ ይችላል።

አገልግሎት የማቅረብ ስራን መጀመር

ብስክሌትን ወይም መኪናን በመጠቀም የአቅርቦት (delivery) አገልግሎት የመስጠት ስራን መጀመር ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ምግብ ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የማድረስ ወይም ደግሞ ለሰዎች ዕቃዎችን በመግዛት ቤታቸው የማድረስ አገልግሎትን መስተት ትችላላችሁ። እንዲህ አይነቱ አገልግሎት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ በእኛዋ አዲስ አበባ ከተማም እየተስፋፋ የመጣ የስራ ዘርፍ ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይ በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ እንደ DoorDash፣ Shipt፣ Uber Eats፣ Amazon Flex እና GrubHub ባሉ ፕላትፎርሞች ላይ በመመዝገብ ነጻ ጊዜን ባገኛችሁ ቁጥር ይኽንኑ ስራ መስራት ትችላላችሁ። ስራችሁ ምግብን፣ ሸቀጣ ሸቀጦችን እና ሌሎች ነገሮችን ወደ ደንበኞች በሮች ማድረስ ይሆናል። ከሬስቶራንቶች ጋር በመገናኘትና በመነጋገር አገልግሎቱን መስጠት ትችላላችሁ። በአገረ አሜሪካ ይኽን አይነቱን አገልግሎት መስጠት በሰዓት እስከ 20 ዶላር ድረስ ያስገኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከተሉት ያሉ አገልግሎቶችን በመቀላቀል በዚህ መንገድ ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ

በትብብር ወይም በቁርኝት የሚሰራ የንግድ ስራ (Affiliate Marketing)

ብዙ የማህበራዊ ሜዲያ ተከታዮች ካፈራችሁ፣ በትብብር ወይም በቁርኝት በሚሰራ የንግድ ስራ (በእንግሊዘኛው Affiliate Marketing በሚባለው ማለት ነው) አማካኝነት ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ። በግንኙነት መስመራችሁ (link) በኩል ለተከናወነ እያንዳንዱ የተሳካ ሽያጭ ኮሚሽን ታገኛላችሁ። ጓደኞቻችሁ ወይም ተከታዮቻችሁ ሊገዙት የሚፈልጉትን ነገር አስቡ፣ ከዚያም ይኽን ሊገዙት የሚፈልጉትን ምርት ወይም አገልግሎት አስተዋውቁ። በውጪው አለም ሰዎች እንደ Amazon Associates፣ ShareASale፣ CJ Affiliate፣ Avangate Affiliate Network እና ClickBank ባሉ የትብብር ወይም የቁርኝት የንግድ ስራ ፕላትፎርሞች ላይ በመመዝገብ የንግድ ስራቸውን ያከናውናሉ። ስለዚህ አሰራር የበለጠ ለማወቅ በትብብር ወይም በቁርኝት የሚሰራ የንግድ ስራ (Affiliate Marketing) የሚለውን ጽሁፋችንን ተመልከቱ።

ዕቃዎችን በምትሸምቱበት ወቅት የ Cashback እና የቅናሽ ሽያጭን መጠቀም

በውጪው አለም ለአብነትም እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት Cashback የሚባል ነገር አለ፤ ይኸውም ምንድን ነው ብትሉ ደንበኞች አንድ የተወሰነ ነገር ሲሸምቱ ለወደፊቱም እንደ ማበረታቻ በማድረግ ሻጮች የሸጡትን ነገር ዋጋ የተወሰነውን ለገዢው ደንበኛቸው የሚመልሱበት አሰራር ነው። ሰዎች ወይም ሸማቾች ይኽን አሰራር በመጠቀም ተመላሽ የሚሆንላቸውን ገንዘብ ይቆጥባሉ፤ እነዚህ ሸማቾች ከ 0.5% እስከ 10% ተመላሽ ያገኛሉ። የዚህ አይነት አሰራር ባሉባቸው አገራት ውስጥ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንም እንደ Swagbucks and Quidco.com ባሉ ፕላትፎርሞች ላይ በመመዝገብ የአሰራሩ ተጠቃሚዎች ለመሆን ትችላላችሁ።

የሌላ ተቀጣሪ ሳይሆኑ ስራን በራስ መስራት ወይም ፍሪላን መጀመር

እንደ Upwork እና Fiverr ባሉ የኦንላይን የፍሪላንስ ፕላትፎርሞች ላይ በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ መስራት ትችላላችሁ። በተለዩ ነገሮች ላይ ለምሳሌ፣ የድረ ገጽ ዲዛይን፣ የመረጃ መፈለጊያ አመቻች፣ ወይም ደግሞ ይዘቶችን የመጻፍ የመሳሰሉ ክህሎቶች ካሏችሁ፣ በፍርላንስ ፕላትፎርም ላይ የጎንዮሽ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ትችላላችሁ። እንደ አንደ የኦንላይን ፍሪላንሰ፣ ለኦንላይን ስራዎች ስታመለክቱ ቀጣሪዎች ሊቀጥሯችሁ ይችላሉ።

በኦንላይን ጽሁፎችን የመጻፍ ስራ

ቤታችሁ ውስጥ ሆናችሁ የጽሁፍ ክህሎታችሁን በመጠቀምና በኦንላይን በመፃፍ ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ። ይኽንን ስራ ለመስራት የሚያስፈልጓችሁ አስተማማኝ የሆነ የበይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት ግንኙነት ያለው ኮምፒውተር፣ ጥሩ የምርምር ክህሎት መኖር እና ለመጻፍ የምትፈልጉባቸውን ርዕሶች በተመለከተ ተገቢ የሆነ እውቀት መኖር ናቸው። የፋይናንስ ባለሙያ ከሆናችሁ፣ በSeeking Alphaላይ በኦንላይን በመፃፍ ገንዘብ ማግኘት ትችላላችሁ። ጽሁፋችሁን Substack newsletterአማካኝነት በማሳተምም ወደ ገንዘብ ልትቀይሩትና ገቢም ለማግኘት ትችላላችሁ።

በኢንተርኔት ኦንላይን ግንኙነት ማስተማር (E-Teaching)

እንደ አሜሪካና ካናዳ በመሳሰሉ አገራት አንድ ሰው የባችለር ዲግሪ እና የስራ ፍቃድ ካለው፣ እንግሊዝኛ ቋንቋን በኦንላይን ለልጆች ማስተማር ይችላል። በቤቱ ተቀምጦና ምቾት እየተሰማውም በሰአት ከ 14-22 ዶላር ያገኛል። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎች ይኽን በኦንላይን የማስተማር ስራ መስራት እንደሚችሉ ግንዛቤው ያላቸው አይመስልም። ከዚህ ይልቅ በስፋት እየተሰራበት ያለው በየልጆች ቤት በመሄድ ከወላጆች ጋር ስምምነት በመፈጸም በሳምንት ለተወሰኑ ቀናትና ሰአታት በገጽ ለገጽ ግንኙነት ማስተማር ነው። ሆኖም ግን፣ እንደ አዲስ አበባ ባሉ በአንጻራዊነት ጥሩ የኢንተርኔት ግንኙነት ባለባቸው አካባቢዎች ጥሩ የቀለም ትምህርቶች እውቀት እና የማስተማር ፍላጎት ካላችሁ እናንተም ልታክናውኑት የምትችሉት ጥሩ ገቢ ማስገኛ ስራ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ VipKid ተብሎ የሚጠራው ፕላትፎርም የማስተማር እቅድን ማየት ትችላላችሁ።

አሮጌ ዕቃዎችን ወይም ቁሳ ቁሶችን በኦንላይን መሸጥ / የማይፈለጉ ዕቃዎችን ወይም ቁሳ ቁሶችን በኦንላይን መሸጥ

የማትጠቀሙባቸውን ዕቃዎች ወይም ቁሳ ቁሶችን በመሸጥ ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ በቤቱ ውስጥ የማያስፈልጓችሁ ወይም የማትጠቀሙባቸው ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ካሉ መሸጥና ገቢ ማግኘት ትችላላችሁ። ዕቃዎቹ ተንቀሳቃሽ ወይም ሞባይል ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር ወይም ታብሌት ሊሆኑ ይችላሉ። ዞር ዞር እያላችሁ ወይም ደግሞ ጎግል በማድረግ የኤሌክክትሮኒክስ ጥገና ወይም አሮጌ ዕቃዎችን የሚገዙ መደብሮችን ፈላልጋችሁ ዕቃዎቹን ወይም ቁሶቹን መሸጥ ትችላላችሁ። ኢትዮጵያ ውስጥም እነዚህን ዕቃዎች ወይም ቁሳ ቁሶች የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ እንደ ፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ መገናኛዎች እና በሌሎችም መላዎች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ እንዳሉ ይታወቃል።

ውሾችን የማንሸራሸር ስራን መስራት

በሰለጠኑት አገራት ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ መስራት ከሚቻልባቸው ስራዎች መካከል አንዱ የሰዎችን ውሾች ማንሸራሸር (ወይም በእንግሊዘኛው Dog walking) ነው። ይኽ ስራ ውሻውን ወይም ወሾቹን ማንሸራሸር፣ መናፈሻ ስፍራ ውስጥ ቁጭ ብለው ወጪ ወራጁን እንዲመለከቱ ማድረግ እንዲሁም ማጫወትን ያካትታል። ስራው ብዙ ባይሆንም ጥቂት ገንዘብን ግን ሊያስገኝ ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ በዙዎች ውሻን የሚወዱ በመሆኑ በየቤታቸው አብረው ያኖሯቸዋል። በእርግጥ ሰዎች በክፍያ ውሾችን የማንሸራሸር ስራ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩም ሲያሰሩም ማየት አልተለመደም፤ ይልቁንም የውሾቹ ባለቤቶች ናቸው ውሾቻቸውን የሚያንሸራሽሩት። አሁን ላይ ግን በተለይ በከተሞች አካባቢ ብዙ ሰዎች በጊዜ መጣበብና በስራ ውጥረት ምክንያት ቢፈልጉም እንኳን ውሾቻቸውን የማንሸራሸር ዕድል አያገኙም። ስለሆነም እናንተ ይኽን ስራ ለመጀመር ቀዳሚዎች የመሆን ዕድልን ልታገኙ ብሎም ስራውን እንደ አንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢ የማግኛ መላ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ።

ፎቶግራፎችን መሸጥ

ፎቶ አንስቶ በኦንላይን የመሸጥ ስራ በሌላው አለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ የመስሪያ አንዱ መላ ነው። እናንተም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ፎቶግራፍ ለማንሳት አስፈላጊ የሆኑት መገልገያ መሳሪያዎች ካሏችሁ፣ ስራውን መጀመር ትችላላችሁ። ስራውን ለመስራት የተራቀቀ ካሜራ ባለቤት መሆን አይጠበቅባችሁም፤ በተንቀሳቃሽ ወይም በሞባይል ስልካችሁ ላይ ባለው ካሜራ መጠቀም ትችላላችሁ። እንደ Shutterstock, iStock and Stocksy የመሳሰሉ የኦንላይን የፎቶግራፍ ፕላትፎርሞች ፎቶዎችን እንደሚገዙ ማወቁ ይጠቅማል።

በቨርቹዋል ዘዴ ማስተማር መጀመር

በአንድ የትምህርት መስክ ላይ ጥሩ እውቀት ካላችሁ፣ ይኽ እወቀታችሁ በአጭር የጊዜ ወሰን ውስጥ ገንዘብ ሊያስገኝላችሁ ይችላል። በርቀት ሆናችሁ ሰዎችን በቨርቹዋል መላ ማስተማሩ ሌላኛው ጥቅሙ ደግሞ የምታስተምሩበትን ዋጋ የምትወስኑትም ራሳችሁ መሆናችሁ ነው። አሁን ላይ የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ በሽታ በመላው አለም አስጊ በሆነበት ሁኔታ ልጆችን በኦንላይን ግንኙነት በማስተማር ገንዘብ መስራት ትችላላችሁ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ የሚያስገኙ ኢንቨስትመንቶችን ማጤን

በፍጥነት ገቢ በሚያስገኙ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተወሰነ የገንዘብ ትርፍን ማግኘት ትችላላችሁ። ብዙ ገንዘብ ማውጣት አያስፈልጋችሁም፤ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ውስን የሆነ የገንዘብ ትርፍንም ማግኘት ልትጀምሩ ትችላላችሁ። የአቻ ለአቻ ብድሮችላይ ገንዘባችሁን ኢንቨስት የምታደርጉ ከሆነ፣ እንደምትጠቀሙበት የአቻ ለአቻ የብድር ፕላትፎርም እስከ 10 ዶላር ድረስ ዝቅ ባለ የገንዘብ መጠን መጀመር ትችላላችሁ። በተፋጠነ ጊዜ የተወሰነ የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት (ምንም እንኳን ለድንገተኛ ጊዜ ፈንድ ተስማሚ ባይሆንም) የሚከተሉትን ኢንቨስትመንቶች ግምት ውስጥ ማስገባት አለባችሁ፡ ክሪፕቶ ኢንቨስትመንት፣ በዝግ አካውንት የሚቀመጥ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ፣ እና የቁጠባ ሂሳብ ወይም አካውንት።

ደሞዝ ወይም ሌላ አይነት ክፍያ ስትወስዱ የሚከፈል ብድር መውሰድ

በድንገተኛ ወይም በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ከሆናችሁና ክሬዲት ካርዶች ወይም ሌላ አማራጭ ከሌላችሁ፣ የግል ብድር (personal loans) ለመውሰድ ማሰብ ትችላላችሁ። ይኽ አይነቱ በአገረ አሜሪካ ውስጥ የሚተረጎመው ተበዳሪዎች ከተለመዱት አይነት (ከመደበኛ) ባንኮች፣ ከብድር ማህበራት ወይም ከኦንላይን አበዳሪዎች በአንድ ጊዜ በብድር መልክ የሚሰጥን ገንዘብ እንደማለት ሆኖ ነው። ለአብነት ያህል፣ በአሜሪካ ደሞዝ ስትወስዱ የምከሉት የብድር አይነት በአንድ አመት የሚኖረው አማካይ የወለድ መጠን 300% በመሆኑ የምትከፍሉት ገንዘብ መጠኑ በታም ከፍተኛ የሚሆን ነው። ስለሆነም፣ አበዳሪዎችን ስትፈልጉ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጥናት ማድረግ እንዲሁም ከከፍተኛ የወለድ ክፍያ ለመዳን ብድሩን በጊዜው እንደምትመልሱ እርግጠኛ መሆን አለባችሁ። እኛ ይህ አይነቱን ብድር እንድትወስዱ የምንመክረው እንደመጨረሻው አማራጭ አድርጋችሁ ነው።

የመደምደሚያ ሃሳቦች

አንዳንድ ጊዜ ገንዘብ በአስቸኳይ በሚያስፈልግበት ሁኔታ ውስጥ ራሳችሁን ልታገኙት ትችላላችሁ። አንዳንድ ጊዜም፣ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው ብድር ማግኘት የሚለው ሃሳብ ነው፤ ይህም ደግሞ ምናልባትም የተሻለው ሃሳብ ላይሆን ይችላል። ከፍተኛ የወለድ መጠን ሊኖራቸው ስለሚችልና በእዳ ወጥመድውስጥ ልትወድቁ የምትችሉበት አጋጣሚም ይዞ ስለሚመጣ ብድር መውሰድ የመጨረሻው አማራጫችሁ ሊሆን ይገባል። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ለመግለጽ እንደሞከርነው ገንዘብን በአጭር የጊዜ ወሰን ውስጥ እና በፍጥነት ልታገኙባቸው የምትችሉባቸው በርካታ ዕድሎች አሉ። በመጨረሻም ግን ልንገልጸው የሚገባው ጉዳይ የወደፊቱን ገንዘብ ነክ ህይወታችሁን የማያዛባውን የተሻለ ገንዘብ በአጭር ጊዜ ሊያስገኝላችሁ የሚችለውን ዕድል እንድትከተሉ ነው።